1 Samuel 2

የሐና የምስጋና ጸሎት

1ሐናም እንዲህ ብላ ጸለየች፤

“ልቤ በእግዚአብሔር ጸና፤
ቀንዴም
በዚህ ስፍራና በቍጥር 10 ላይ ቀንድ የጥንካሬ ምልክት ነው።
በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ፤
አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ፤
በማዳንህ ደስ ይለኛልና።

2“እንደ እግዚአብሔር ያለ ቅዱስ
ወይም አንድ ቅዱስ
ማንም የለም፤
ከአንተም በቀር ሌላ የለም፤
እንደ አምላካችን ያለ ዐለት የለም።

3“ይህን ያህል በመታበይ አትናገሩ፤
እንዲህ ያለውም የእብሪት ቃል ከአፋችሁ አይውጣ፤
እግዚአብሔር አምላክ ዐዋቂ ነውና፤
ሥራም ሁሉ በእርሱ ይመዘናል።

4“የኀያላን ቀስቶች ተሰባብረዋል፤
ደካሞች ግን በኀይል ታጥቀዋል።
5ጠግበው የነበሩ ለእንጀራ ሲሉ ተገዙ፤
ተርበው የነበሩ ግን እንጀራ ጠገቡ፤
መካኒቱ ሰባት ልጆች ወልዳለች፤
ብዙ ወንዶች ልጆች ወልዳ የነበረችው ግን መከነች።

6እግዚአብሔር ይገድላል፤ ያድናልም፤
ወደ መቃብር
ዕብራይስጡ ሲኦል ይላል
ያወርዳል፤ ያወጣልም።
7 እግዚአብሔር ያደኸያል፤ ያበለጽጋልም፤
ያዋርዳል፤ ከፍ ከፍም ያደርጋል።
8እርሱ ድኻውን ከትቢያ ያነሣል፤
ምስኪኑንም ከጕድፍ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤
ከመኳንንቱ ጋር ያስቀምጣቸዋል፤
የክብር ዙፋንም ያወርሳቸዋል።

“የምድር መሠረቶች የእግዚአብሔር ናቸውና፣
ዓለምን በእነርሱ ላይ አድርጓል።
9እርሱ የቅዱሳኑን እግር ይጠብቃል፤
ክፉዎች ግን በጨለማ ውስጥ ይጣላሉ።

“ሰው በኀይሉ ድል አያደርግም፤
10 ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቃሉ፤
እርሱ ከሰማይ ያንጐደጕድባቸዋል፤
እግዚአብሔር እስከ ምድር ዳርቻ ይፈርዳል።

“ለንጉሡ ኀይልን ይሰጣል፤
የመሲሑንም ቀንድ ከፍ ከፍ ያደርጋል።”
11ከዚያ በኋላ ሕልቃና ወደ ቤቱ ወደ ራማ ሄደ፤ ብላቴናው ግን በካህኑ በዔሊ ፊት እግዚአብሔርን ያገለግል ነበር።

የዔሊ ልጆች ክፉ ድርጊት

12የዔሊ ልጆች ምናምንቴዎች ነበሩ፤ እግዚአብሔርንም አይፈሩም ነበር። 13በዚያን ጊዜ ካህናቱ ከሕዝቡ ጋር ባላቸው ግንኙነት የሚፈጽሙት ወግ ነበር፤ ይኸውም ማንም ሰው መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ፣ ሥጋው እየተቀቀለ ሳለ የካህኑ አገልጋይ ሦስት ጣት ያለውን ሜንጦ ይዞ ይመጣል፤ 14ወደ ድስቱ ወይም ወደ ቶፋው ወይም ወደ አፍላሉ፣ ወይም ወደ ምንቸቱ ይሰደዋል። ከዚያም ካህኑ ሜንጦው ያወጣውን ማናቸውንም ሥጋ ለራሱ ይወስደዋል። ወደ ሴሎ የሚመጡትን እስራኤላውያን ሁሉ የሚያስተናግዱት በዚህ ዐይነት ነበር። 15ነገር ግን ሥቡ ገና ከመቃጠሉ በፊት የካህኑ አገልጋይ መጥቶ መሥዋዕት የሚያቀርበውን ሰው፣ “ካህኑ ጥሬውን እንጂ የተቀቀለውን ሥጋ ከአንተ ስለማይቀበል፣ ለካህኑ የሚጠበስ ሥጋ ስጠኝ” ይለው ነበር።

16ሰውየውም፣ “በመጀመሪያ ሥቡ ይቃጠል፤ ከዚያ በኋላ የምትፈልገውን ትወስዳለህ” ቢለው እንኳ አገልጋዩ፣ “አይሆንም፤ አሁኑኑ ስጠኝ፤ ያለዚያ በግድ እወስዳለሁ” ይለው ነበር።

17 ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን መሥዋዕት ይንቁ ስለ ነበር
ወይም የሚንቁ ሰዎች ስለ ነበሩ
፣ ይህ የወጣቶቹ ኀጢአት በእግዚአብሔር ፊት እጅግ ታላቅ ነበረ።

18ብላቴናው ሳሙኤል ግን ከበፍታ የተሠራ ኤፉድ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት ያገለግል ነበር። 19እናቱም ከባሏ ጋር ዓመታዊ መሥዋዕት ለማቅረብ በምትሄድበት ጊዜ ሁሉ ትንሽ መደረቢያ እየሠራች ይዛለት ትሄድ ነበር። 20ዔሊም፣ “በጸሎት ባገኘችውና ለእግዚአብሔር በሰጠችው ልጅ ምትክ እግዚአብሔር ከዚህችው ሴት ዘር ይስጥህ” እያለ ሕልቃናንና ሚስቱን ይመርቃቸው ነበር፤ ከዚያ በኋላ ወደ ቤታቸው ይመለሱ ነበር። 21እግዚአብሔርም ሐናን ባረካት፤ ፀነሰችም፤ ሦስት ወንዶች፣ ሁለት ሴቶች ልጆችም ወለደች። ብላቴናውም ሳሙኤል በእግዚአብሔር ፊት አደገ።

22በዚህ ጊዜ ዔሊ እጅግ አርጅቶ ነበር፤ ልጆቹም በመላው እስራኤል ያደርጉ የነበረውን፣ በመገናኛውም ድንኳን ደጃፍ ከሚያገለግሉ ሴቶች ጋር ዝሙት መፈጸማቸውን ሰማ። 23ስለዚህም እንዲህ አላቸው፤ “ስለምትፈጽሙት ክፉ ድርጊት ከመላው ሕዝብ እሰማለሁ፤ ለምን እንዲህ ያለ ነገር ታደርጋላችሁ? 24ልጆቼ ሆይ፤ ትክክል አይደላችሁም፤ በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል ተሠራጭቶ የምሰማባችሁ ወሬ ጥሩ አይደለም። 25አንድ ሰው ሌላውን ቢበድል፣ እግዚአብሔር
ወይም መሳፍንት
ጣልቃ ገብቶ ይፈርዳል፤ ነገር ግን ሰው እግዚአብሔርን ቢበድል፣ ማን ይማልድለታል?” ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ስለ ፈለገ፣ ልጆቹ የአባታቸውን ተግሣጽ አልሰሙም።

26ብላቴናውም ሳሙኤል በአካልና በሞገስ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት እያደገ ሄደ።

በዔሊ ቤተ ሰብ ላይ የተነገረ ትንቢት

27በዚህ ጊዜ አንድ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ዔሊ መጥቶ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘የአባትህ ቤት በግብፅ ምድር በፈርዖን እጅ በነበረ ጊዜ ራሴን ገለጥሁለት? 28የእኔ ካህን እንዲሆን፣ ወደ መሠዊያዬ እንዲወጣ፣ ዕጣን እንዲያጥን፣ በፊቴም ኤፉድ እንዲለብስ ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ አባትህን መረጥሁት። ደግሞም እስራኤላውያን በእሳት የሚያቀርቡትን ቍርባን ሁሉ ለአባትህ ቤት ሰጠሁ። 29ታዲያ በማደሪያዬ እንዲቀርብ ያዘዝሁትን መሥዋዕትና ቍርባን የናቃችሁ ለምንድን ነው? አንተና ልጆችህ ሕዝቤ እስራኤል ካቀረበው ቍርባን ሁሉ ምርጥ ምርጡን በልታችሁ ራሳችሁን በማወፈር ከእኔ ይልቅ ልጆችህን የምታከብራቸው ስለ ምንድን ነው?’

30“ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ቤትህና የአባትህ ቤት በፊቴ ለዘላለም ያገለግሉኝ ዘንድ ተስፋ ሰጥቼ ነበር፤’ አሁን ግን እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ይህን ከእንግዲህ አላደርገውም፤ የሚያከብሩኝን አከብራለሁ፤ የሚንቁኝም ፈጽሞ ይናቃሉ። 31እነሆ፤ በዘርህ ሽማግሌ እንዳይገኝ ያንተን ኀይልና የአባትህን ቤተ ሰብ ኀይል የምሰብርበት ጊዜ ይመጣል፤ 32በማደሪያዬም መከራ ታያለህ፤ ምንም እንኳ ለእስራኤል በጎ ነገር ቢደረግም፣ በቤተ ሰብህ ውስጥ ሽማግሌ ፈጽሞ አይገኝም። 33ከመሠዊያዬ የማላስወግዳቸው ዘሮችህ በሕይወት የሚተርፉትም ዐይኖችህን በእንባ ለማፍዘዝ፣ ልብህን በሐዘን ለማደንዘዝ ብቻ ነው፣ ሌሎቹ ዘሮችህ ግን በሙሉ በለጋነታቸው በዐጭር ይቀጫሉ።

34“ ‘በሁለቱ ልጆችህ በአፍኒንና በፊንሐስ ላይ የሚደርሰው ላንተ ምልክት ይሆንሃል፣ ሁለቱም በአንድ ቀን ይሞታሉ። 35እንደ ልቤና እንደ አሳቤ የሚያገለግል የታመነ ካህን ለራሴ አስነሣለሁ፤ ቤቱን አጽንቼ አቆማለሁ፣ እርሱም በቀባሁት ፊት ለዘላለም ያገለግላል። 36ከዘሮችህም መካከል የተረፈው ማንኛውም ሰው፣ ለአንዲት ጥሬ ብርና ለቍራሽ እንጀራ ሲል በፊቱ ወድቆ ይሰግዳል፤ “የዕለት ጕርሴን እንዳገኝ እባክህ በማንኛውም የክህነት ሥራ ላይ መድበኝ” በማለት ይለምናል።’ ”

Copyright information for AmhNASV